- በህግ ተለይተው በክልሉ መንግሥት እንዲሰበሰቡ የተመደቡትንና ከፌዴራሉ መንግሥት በሚሰጠው ውክልና መሠረት በክልሉ መንግሥት እውቅና የፌዴራሉንና የጋራ ገቢዎችን ይወስናል፣ ይሰበስባል፣
- በክልሉ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን የታክስ ሥርዓት ማሻሻያ ኘሮግራም አፈጻጸም በባለቤትነት ይመራል፣ ያስተባብራል፣
- የታክስ ህጐችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉትንና በማናቸውም ሰው እጅ የሚገኙ ሰነዳችን ይመረምራል፣
- ታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ ታክስ በፈቃደኝነት የመክፈል ባህልን እንዲያዳብርና መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ እንዲረዳ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨባጫ መድረኮች ትምህርት እንዲሰጥ ያደርጋል፣
- የታክስ አስተዳደር ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት የሚያስችለውን የስልጠናና የሙያ ማሻሻያ ስልቶች ይዘረጋል፣
- የታክስ ህጐችን በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ይመረምራል፣ ይከሳል፣ ይከራከራል፣ ይህንኑ ለማከናወን የራሱን ዐቃቢያነ-ህግና የታክስ ወንጀል መርማሪዎች ያደራጃል፣ አፈጻጸማቸውን ይቆጣጠራል፣
- በክልሉ ውስጥ ዘመናዊ የታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ ያደርጋል፣ በመስኩ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ይሰጣል፣ ታክስ ነክ መብቶች በአግባቡ እንዲፈጸሙ ያደርጋል፣
- በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ የገቢ ጥናቶችን ያካሂዳል
- በተሻሻለው የአማራ ብሔራዊ ክልል ከተሞች ማቋቋሚያ፣ ማደራጃና ሥልጣንና ተግባራት መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 91/1996 ዓ.ም. መሠረት ለከተማ አስተዳደሮች የተሰጠው የፊስካል ነጻነት እንደተጠበቀ ሆኖ በከተማ አስተዳደሮች ሥልጣን ሥር የሚሸፈኑ የአገልግሎት ገቢዎችን ይወስናል፣ ይሰበስባል፣ የሙያ ድጋፍ ይሰጣል
- ከዚህ በላይ በተራ ቁጥር/10/ የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ የከተማ ማዘጋጃ ቤቶችን ገቢ ይወስናል፣ ይሰበስባል፣ የሙያ ድጋፍ ይሰጣል፣
- ለታክስ አወሳሰን የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ያሰባስባል፣ ያጠናክራል፤ እነዚህኑ በመጠቀም ታክስ ይወስናል፣ ይሰበስባል፣
- የታክስ ህጐችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማውጣትና ማሻሻል፣ ሲያስፈልግ ጥናቶችን ያካሂዳል፣ ለክልሉ መንግሥት አቅርቦ ያስወስናል፣
- የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ ውል ይዋዋላል፣ በስሙ ይከሳል፣ ይከሰሳል፣
- ለታክስ ከፋዩ አማራጭ የታክስ መክፈያ ተቋማትን ያመቻቻል፣
- የመሥሪያ ቤቱን የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድና በጀት አዘጋጅቶ ያቀርባል፣ ሲፈቀድለትም ተግባራዊ ያደርጋል፣ የሥራ እንቅስቃሴዎቹን በሚመለከት ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ወቅታዊ ሪፖርቶችን ያቀርባል፣
- የታክስ ወንጀሎችን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣኑን እንደአስፈላጊነቱ ለክልሉ ፖሊስ እና የዐቃቢ ህግ አካላት በውክልና ሊሰጥና ሊያሰራ ይችላል፣
- ዓላማዎችን ለማስፈጸም የሚረዱ ሌሎች በህግ የተፈቀዱ ተግባራትን ያከናውናል፡፡