በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ገቢዎች መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት ከመደበኛ ገቢ ብር 727,456,400 እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ ብር 309,959,734 በድምሩ ብር 1,037,416,134 ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ

እስከ የካቲት 30/2016 ዓ/ም ድረስ ከመደበኛ ገቢ ብር 353,818,443.41 ወይም 48.60 በመቶ እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ ብር 69,289,125.76 ወይም 22.4 በመቶ በድምሩ ብር 423,107,569.2 ወይም 40.78 በመቶ ገቢ መሰብሰቡን ከመምሪያው ማህበራዊ ገፅ የተገገኘ መረጃ አመላክቷል።

ገቢው አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው 342,038,662.29 ብር ጋር ሲነፃጸር የብር 81,068,906.9 ወይም የ23.7 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን መረጃው ያመላክታል።

ይህ ገቢ በንፅፅር የተሻለ ቢመስልም፣ በ2016 በጀት ዓመት ለማሳካት ከታቀደውና በዚህ ወቅት ላይ በጤናማ የዕቅድ አፈፇፀም መድረስ ከነበረበት አኳያ ሲመዘን ግን ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ መረጃው ያሳያል።

ለገቢ አሰባሰቡ ማነስ ዋና ዋና ምክንያቶች፡- ያለደረሰኝ ግብይት፣ የሀሰተኛ ደረሰኝ ሥርጭት፣ የህገ-ወጥ ንግድ መስፋፋት፣ ከ2015 የቀን ገቢ ጥናት ጋር ተያይዞ የቅሬታዎች እና የይግባኝ ጥያቄዎች መብዛትና በዚህ ወቅት ላይ ያልተከፈለ ታክስ/ግብር ክምችት መኖር እንዲሁም በክልሉ ውስጥ የተከሰተው የፀጥታ ችግር ተግዳሮቶች እንደሆኑ መረጃው አመላክቷል።

በተመዘገበው አፈፃፀም የወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ድርሻ ሲታይ፣ ባቲ ዙሪያ ወረዳ 55.5% ፣ ደዋ ጨፋ ወረዳ 53.75%፣ ጂሌ ጥሙጋ ወረዳ 52.69%፣ ደዌ ሀረዋ ወረዳ 48.70%፣ አርጡማ ፉርሲ ወረዳ 40.60 % ፣ ባቲ ከተማ 40.40% ፣ ከሚሴ ከተማ 39.65 %፣ ጨፋ ሮቢት ከተማ 28.14%፣ ሰንበቴ ከተማ 25.5% ከዓመቱ እቅዳቸው መፈፀማቸው ታውቋል።

am