ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የታክስ ሰርዓቱን ለማዘመን የወረቀት አሰራሮችን የሚያስቀር የኤሌክትሮኒክስ ኢንቮይስ ሲስተም አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ሠነድ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ተፈራርሟል::
ስምምነቱን የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትግስት ሀሚድ ፈርመዋል::
በስምምነቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በህገ-ወጥ ንግድ በቀረጥ እና ታክስ ማጭበርበር ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰብሰብ ያለበትን ገቢ ለመሰብሰብ አለመቻሉን አመላክተው ይህ ስርዓት የግብይት ደረሰኝን ከአንድ አካል ብቻ ማለትም ከገቢዎች ሚኒስቴር ብቻ እንዲቆረጥ በማድረግ በሃሰተኛ ደረሰኝ የሚደረግ ማጭበርበርን የሚያስቀር ነው ብለዋል::
ሚኒስተሯ ስርዓቱ ለነጋዴው ማሕበረሰብም ሆነ ለሸማቹ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረው የነጋዴው ማህበረሰብ ለደረሰኝ ሕትመት የሚያወጣውን ወጪና ጊዜ ከማስቀረቱም በላይ የግብይት ሂደቱን በቀጥታ ለመከታተልና ለመቆጣጠርም እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትግስት ሀሚድ በበኩላቸው የሚዘረጋው የኤሌክትሮኒክስ ኢንቮይስ ሲስተም ስርዓት የማንዋል የደረሰኝ አስተዳደር ስርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክስ የደረሰኝ አስተዳደር ስርዓት መቀየር የሚያስችል እንዲሁም የዲጂታል ግብይት ስርዓቱን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳልጥ መሆኑን አንስተው የሚዘረጋው ስርዓት ውጤታማ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል::